የሰሜን ወሎ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ። (ሰሜን ወሎ ከመል- ወልዲያ ሐምሌ 4/2017 ዓ/ም).የሰሜን ወሎ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም የበጀት ዓመቱን ዓመታዊ የቁልፍ እና ዓበይት የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን አካሂዷል። ግምገማው በመምሪያው ስር ባሉ ሁሉም የሥራ ቡድኖች የ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸምን የዳሰሰ ሲሆን በግምገማው ወቅት በመምሪያው ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተገኙ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና በቀጣይ ሊተገበሩ የሚገባቸው የማስተካከያ እርምጃዎች በዝርዝር ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በበጀት ዓመቱ ለ117 ፕሮጀክቶች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሥራ ላይ መዋሉ ተገለጸ፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ከ117 ፕሮጀክቶች መካከል 97ቱን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሥራ ላይ ማዋሉን የሰሜን ወሎ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪየ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ መኮንን የሱፍ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከተሞችን ፅዱ፣ሳቢና ማራኪ በማድረግ ለኑሮ ተስማሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በመደበኛና በኮሪደር ልማት በርካታ ስራዎች መሥራት ተችሏል ብለዋል፡፡ በዞኑ ካሉ ከ117 ፕሮጀክቶች መካከል 97ቱን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ከ 600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማድረግ ተችሏል ያሉት ኃላፊው 20 ቀሪ ፕሮጀክቶች በሥራ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የተሠሩት ፕሮጀክቶች የውሃ ማስወገጃ (ማፋሰሻ) ካናል፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የመብራትና የውሀ መስመር ዝርጋታ፣ የጠጠር መንገድ ሴራሚኮች፣ የተቋማትና የዝቅተኛ ነዋሪዎች ቤት ግንባታ እንዲሁም የአረንጓዴ ቦታና የመዝናኛ ግንባታዎች ናቸውም ብለዋል፡፡ በዞኑ ካሉት 6 ከተማ አስተዳደሮች መካከል በ3 ከተማ አስተዳደሮች ላይ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው በመርሳ ከተማ 4 ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ግራና ቀኝ ማስፋፋት ሥራ ከ 400 ሚሊዮን ብር በላይ በሥራ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በቆቦ ከተማ 600 ሜትር የአስፓልት ግራና ቀኝ ማስፋፋት ሥራ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎ 80 በመቶ አፈፃፀም ላይ የደረሰ ሲሆን በጋሸና ከተማ 700 ሜትር ርዝመት ያለው የአቨረንጓዴ ቦታ ማስዋብ ስራ በ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡ ሃላፊው ከ 427 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ለኮሪደር ልማት ብቻ መዋሉን አክለው ገልፀዋል፡፡

በክልልና በወረዳ በጀት በማህበረሰብ ተሳትፎ ፣ በውጭና በሀገር ውስጥ በሚኖሩ አጋር አካላት፣ ከከተሞች ከራሳቸው ገቢና በመቀናጆ ፕሮጀክቶች የተሰሩ መሆናቸውንም አቶ መኮንን አብራርተዋል፡፡ በዘርፉ ለ19 ሺህ 512 የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ ዕድል ለመፍጠር በዕቅድ ተይዞ ለ 24 ሺህ 516 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ (መረጃው የሰሜን ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን ነው).